Tedla Fantaye
Tedla Fantaye

Obituary of Tedla Fantaye

 

የአቶ ተድላ ፋንታዬ የሕይወት ታሪክ።

 

                አቶ ተድላ ፋንታዬ ከእናታቸው ከወይዘሮ ዘርፍነሽ ወልደየስና ከአባታቸው ከመምሬ ፋንታዬ ወልደሚካኤል በቀድሞው የአርሲ ጠቅላይ ግዛት በጭላሎ አውራጃ ልዩ ስሙ ከታር ገነት ጎልጃ በሚባል ስፍራ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር የካቲት 12 ቀን 1944 ዓመተ ምሕረት (አንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር Feburary 19, 1944) ተወለዱ።

 

            እድሜያቸው ለትህምርት እንደደረሰም በመንፈሳዊ ት/ቤት ፊደል በመቁጠር ዳዊት ከደገሙ በሗላ ከልጅነታቸው ጀምረው ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔር ፍቅር ያደረባቸውና ፈሪሃ እግዚአብሔር የነበራቸው በመሆኑ የድቁና ማእረግ ተቀብለው ባደጉበትና መንፈሳዊ ትምሕርት በተማሩበት በዚያው በጭላሎ አውራጃ ጢዮ ወረዳ ዱግድአ ቀበሌ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለአጭር ጊዜ በድቁና አገልግለዋል። ከዚያም በራሳቸው አነሳሺነት በጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ አሰላ በሚገኘው ራስ ዳርጌ ት/ቤት ዘመናዊ ትምሕርት ጀምረው የአንደኛና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው በዳግማዊ ምኒልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀዋል።

 

            የአቶ ተድላ ፋንታዬ ወላጆች በግብርና ሙያ ይተዳደሩ ስለነበርና ያፈሩዋቸውን 12 ልጆች በችግር እያሳደጉ መሆናቸውን በቅርብ ስለተረዱ ከፍተኛ ትምህርት የመቀጠል ዐላማቸውን አቋርጠው በ1957 ዓመተ ምህረት (በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1965) በኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበር (ኢ.ሠ.አ.ማ  CELU) ጽ/ቤት ስራ ጀመሩ።

 

በማህበሩ ጽ/ቤት ይሠሩ በነበረበት ጊዜ ስለ ሠራተኛ ማህበራት አደረጃጀት፣ ስለ አለም አቀፍ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግጋት፣ ስለ ሠራተኞች ሕጋዊ መብት አከባበር፣ ስለ ሕብረት ስምምነት ድርድር፣ ስለ ሠራተኞች ማህበራት ትምህርት አሰጣጥና ስለ ስነ ጽሁፍ ዝግጅት አገር ውስጥ በተካሄዱ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ሴምናሮች ተካፍለዋል። በተጨማሪም አውሮፓ በሚገኘው የአለም ነጻ ሠራተኞች ማህበር በአሜርካ ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው African American Labor Center (AALC)፣ New Jersey በ Rutgers University እና Maryland በሚገኘው George Meany Labor College እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1971 ሠራተኛ ነክ ኮርሶችን ተከታትለው የምስክር ወረቀቶችና ዲፕሎማዎች ተቀብለዋል።

 

አቶ ተድላ በኢ ሠ ማ ጽ/ቤት በሠሩባቸው 28 አመታት በሕግ እና በቅሬታ ማስፈጸሚያ፣ በትምህርትና ማስታወቂያ፣ በጠቅላላ አገልግሎት ክፍሎች ረዳት ሃላፊነት፣ በሠራተኛ ድምጽ ወርሃዊ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ሃላፊነት፣ በማህበራት ማደራጃ ዋና ክፍል ሃላፊነት በቅንነት አገልግለዋል።

 

            ወታደራዊው መንግስት (ደርግ) ሥልጣን አንደያዘም በሠራተኛው ላይ ሲፈጸም የነበረውን ኢዲሞክራሲያዊ አሠራር ከሠራተኛው ጋር ሆነው ለመብቱ መከበር በመታገላቸው፣ መጀመሪያ በመስከረም ወር 1968 ዓመተ ምህረት ከበርካታ የማህበራት መሪዎች ጋር ታስረው ራሳችው እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ለ 6 ወራት ከፍተኛ ስቃይን አሳልፈዋል። በአቶ ተድላና በሌሎችም የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበራት መሪዎች ያለ ፍርድ መታሰር የተቆጣው የኢቶዮጵያ ላብ አደር ባካሄደው አገር አቀፍ ተቃውሞና በወሰደው የሥራ ማቆም እርምጃ ከእሥር ተለቀው ወደ ሥራቸው ቢመለሱም፣ ወታደሪዊው መንግሥት ሠራተኛውን ለአመጽ ያነሳሱብኛል በሚል ስጋት በግንቦት ወር 1968 ዓመተ ምህረት የፋብሪካ ኢንዱስትሪ ሠራተኞች ማህበር ምሥረታ ላይ መደበኛ የማደራጀት ሥራቸውን ሲያከናውኑ ለሁለተኛ ጊዜ በደርግ አፋኞች ተይዘው በሚስጥር

በተሠጠ ውሳኔ ለ 5 ዓመታት የመከራና የስቃይ ሕይወት በታላቁ ቤተመንግሥት ውስጥ በነበረው ማቆያና በዓለም በቃኝ እሥር ቤት የእሥር ጊዜያቸውን ጨርሰው ወጥተዋል።

 

ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን በሀይል ሲገዛ የነበረው ወታደራዊው መንግሥት በሕዝብ ትግል በመዳከሙ በግንቦት ወር 1983 ዓመተ ምህረት ሥልጣን የጨበጠው የ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. አስተዳደርም ብዙ ሳይቆይ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ለገንዘብ ሚኒስቴር በተጻፈ ደብዳቤ በደርግ አስተዳደር ወቅት የተቋቋሙ መንግሥታዊና የሕዝባዊ ድርጅቶች ንብረትና ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና እንዲዛወር መታዘዙን ለ ኢ.ሠ.ማ ጽ/ቤት በግልባጭ የደረሠወን ደብዳቤ አቶ ተድላ እንደተመለከቱ የዋና ጽ/ቤቱንና የኢንድስቱሪ ሠራተኛ ማህበራት ጽ/ቤቶችን ቋሚ ሠራተኞች በማስተባበር ጊዜያዊ ኮሚቴ ካቋቋሙ በኋላ የህዝብ ጥሬ ገንዘብና ንብረትን ወደ መንግስት ማዛወር አግባብ እንዳልሆነና በተለይም ኢ.ሠ.ማ.ን እና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን እንደማይመለከት ጠንከር ያለ ደብዳቤ ለጠቅላ ሚኒስቴሩ ጽ/ቤት በመጻፋቸው በሠራተኛ ማህበራቱ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ እንዲሻር አድርገዋል።

 

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ቀጣይነቱ ታውቆ በአገር አቀፍ ደረጃ እስከሚዋቀርና አመራሩን የሠራተኛው ተመራጮች እስከሚረከቡ ድረስ፣ የዋናው ጽ/ቤትና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ቋሚ ሠራተኞችና ንብረቶቻቸው በነበሩበት ሁኔታ እንዲቆዩ የሚያስተባብር አገር አቀፍ ጊዜያዊ የሠራተኞች ኮሚቴ ሲቋቋዋም ሁሌም የሠራተኛውን ድምጽ ሲያሰሙ የነበሩት አቶ ተድላ የ ኢ.ሠ.ማ.፣ ጊዜያዊ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ሆነው ስለተመረጡ የተሠጣቸውን ሃላፊነትና የተቀበሉትን ከባድ አደራ በአግባቡ ለመወጣት ከሌሎች የኮሚቴው አባላት ጋር ሆነው አገር አቀፍ የ ኢ.ሠ.ማ. አስመራጭ ኮሚቴ እስኪቋቋም ድረስ ያደረጉት ጥረት ቀላል አልነበረም። በተለይም የሠራተኛ ማህበራት በክልል እንዲዋቀሩ በአገር አቀፉ የሠራተኞች ጉባኤ ላይ የሠራተኛ መሪዎች ነን ከሚሉ ጥቅም አደሮች የቀረበውን ሃሳብ በጽኑ ተቃውመው ሠራተኞች በሙያቸው እየተሰባሰቡ አገር አቀፍ ማህበራቸውን (ኢ.ሠ.ማ. ን) እንዲያቋቋሙ በጉባኤው ላይ ያሰሙት ንግግር ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ በመሆኑ እስካሁንም በዛው ቀጥሎ ይገኛል።

 

ይህ በዚህ እያለ African American Labor Center (AALC) ለ ኢ.ሠ.ማ. ጽ/ቤት በላከው የጥሪ ደብዳቤ አንድ ሰው ለኮርስ እንዲላክለት በጠየቀው መሰረት በነበረው የ ኢ.ሠ.ማ. ጊዜያዊ ኮሚቴ ተመርጠው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በJuly 1993 (ማለትም በ 1985 ዓመተ ምህረት) ወደ አሜርካ ከመጡ በኋላ የመጡበትን ኮርስ ጨርሰው ከቤተሰብና ከቅርብ ጓደኞቻቸው የተሰጣቸውን ምክር በመቀበል አሜርካ ጥገኝነት ጠይቀው ያለምንም ውጣውረድ ተቀባይነት አግኝተዋል።

 

ከዚያም በየተራ ቤተሰቦቻቸውን ወደ አሜርካ ካስመጡ በኋላ Washington DC 5 ዓመታት ቆይተው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ July 1998 ወደ ሻርለት በመዛወር ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመግባባትና በመተባበር በተላያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ጉልህ ተሳትፎ አድርገዋል። በ November 1998 በሻርለት ቤተክርስትያን ለማቋቋም እንቅስቃሴ ሲደረግ ከመሥራቾቹ አንዱ በመሆን ከማገልገላቸውም በላይ በዚሁ ከተማ የታመሙ በመጠየቅና የተቸገሩ በመርዳት፣ በአገር ቤትም ለተቸገሩ ወገኖች፣ ለአብነት ት/ቤት ተማሪዎች፣ ለአብያተ ክርስቲያናት፣ እንዲሁም ህጻናት ለሚያሳድጉ ድርጅቶች ከነቤተሰቦቻቸው እርዳታ ሲያደርጉ የነበሩ ሰው ናቸው።

 

            አቶ ተድላ “ሌሎችን በመርዳትና በማገዝ ውስጥ እራሳችንን እንረዳለንና ከእኛ የወጣው መልካምነት ዞሮ ዞሮ ወደኛው ይመጣል” የሚለውን አባባል ታመው በነበረበት አስቸጋሪ ጊዜ በአካባቢውና በተለያዩ አገራት በሚኖሩ ሠዎች የተደረገላቸውን ጥያቄና ልባዊ ትብብር በማየት ለማረጋገጥ ተችሏል።

 

            አቶ ተድላ የሰባት ልጆች አባትና የ 13 ታድጊዮች አያት ነበሩ።

 

            እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ከደጋጎቹ ጎን ያሳርፍልን። አሜን

 

 

 

 

Tedla Fantaye was born on February 12, 1944, in the old Arsi province, Ketar Golja.

 

When he was old enough for school, he spent a short time at St. Michael's Orthodox Tewahedo Church in the Chelalo district of the Arsi province where he grew up and received spiritual education. Then, at his own initiative, he started high school in Ras Darge School in the capital of Arusi, Asela. Afterward, he completed secondary education at Menelik II Secondary School in Addis Ababa.

 

Since the parents of Mr. Tedla Fantaye had been living on a farm, he soon realized they were raising 12 children who needed his support. Therefore, he stopped his pursuit of higher education and began working at the Confederation of Ethiopian Labor Unions (CELU) office in 1965.

 

While working at the union office, he participated in regional and international seminars on the organization of trade unions, international labor laws and rights, collective bargaining, and educational enhancement of labor unions. In addition, Mr. Tedla attended workshops at Rutgers University (New Jersey), and the Meyer Labor College (Maryland).

 

During his 28 years in the office, Mr. Tedla faithfully served in multiple departments including workers’ satisfaction, general services, the editorial staff of monthly magazines, and the central department.

 

In July of 1993, the African American Labor Center (AALC) invited Mr. Tedla to attend a seminar in representing the Ethiopian Employee Association in the USA. Once he finished the course, his friends and family advised him to settle in the states for better education opportunities for his kids.

 

After relocating his family to Washington D.C., they lived there for five years before moving to Charlotte, NC in July of 1998. In Charlotte, Mr. Tedla became involved in various social issues while interacting with the Ethiopian community. Among his contributions, he is best known for being one of the founders of the Ethiopian Orthodox Church of Charlotte in November of 1998. He was highly regarded for strengthening a close-knit community in Charlotte; Mr. Tedla was also known for his generosity in supporting children raised to be missionaries, churches, and impoverished families in Ethiopia.

 

Mr. Tedla's favorite motto is “The moment when you do good for others, good things come back to you.” It became evident during his illness when he was surrounded and cared by many friends and family members. His motto inspired his seven children, 13 grandchildren, and anyone who knew Mr. Tedla. May God rest his soul in Heaven. Amen.

 

 

Mourners are welcome to leave condolences for the family via the guestbook provided.

Tuesday
12
May

Funeral Service

10:00 am - 12:30 pm
Tuesday, May 12, 2020
Holy Trinity Ethiopian Orthodox Tewahedo Church
9420 Idlewild Road
Charlotte, North Carolina, United States
Tuesday
12
May

Interment

1:00 pm - 1:30 pm
Tuesday, May 12, 2020
Charlotte Memorial Gardens
7632 Hood Road
Charlotte, North Carolina, United States
704-536-2374
Share Your Memory of
Tedla